Tuesday, February 16, 2010

መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ

ምዕራፍ 1።

1፤ ንጉሡ ዳዊትም ሸመገለ ዕድሜውም በዛ፤ ልብስም ደረቡለት፥ ነገር ግን አይሞቀውም ነበር።

2፤ ባሪያዎቹም። ለጌታችን ለንጉሡ ድንግል ትፈለጋለች፤ በንጉሡም ፊት ቆማ ታገልግለው፥ በጌታችንም በንጉሡ ብብት ተኝታ ታሙቀው አሉት።

3፤ በእስራኤልም አገር ሁሉ የተዋበች ቈንጆ ፈለጉ፤ ሱነማይቱን አቢሳንም አገኙ፥ ወደ ንጉሡም ይዘዋት መጡ።

4፤ ቈንጆይቱም እጅግ ውብ ነበረች፤ ንጉሡንም ትረዳውና ታገለግለው ነበር፥ ንጉሡ ግን አያውቃትም ነበር።

5፤ የአጊትም ልጅ አዶንያስ። ንጉሥ እሆናለሁ ብሎ ተነሣ፤ ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን በፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎች አዘጋጀ።

6፤ አባቱም ከቶ በሕይወቱ ሳለ። እንዲህ ለምን ታደርጋለህ? ብሎ አልተቈጣውም ነበር፤ እርሱ ደግሞ እጅግ ያማረ ሰው ነበረ፤ ከአቤሴሎምም በኋላ ተወልዶ ነበር።

7፤ ሴራውም ከጽሩያ ልጅ ከኢዮአብና ከካህኑ ከአብያታር ጋር ነበረ፥ እነርሱም አዶንያስን ተከትለው ይረዱት ነበር።

8፤ ነገር ግን ካህኑ ሳዶቅና የዮዳሄ ልጅ በናያስ ነቢዩም ናታን ሳሚም ሬሲም የዳዊትም ኃያላን ከአዶንያስ ጋር አልነበሩም።

9፤ አዶንያስም በጎችንና በሬዎችን ፍሪዳዎችንም በዓይንሮጌል አጠገብ ባለችው በዞሔሌት ድንጋይ ዘንድ ሠዋ፤ የንጉሡንም ልጆች ወንድሞቹን ሁሉ፥ የንጉሡንም ባሪያዎች፥ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ጠራ።

10፤ ነገር ግን ነቢዩን ናታንን፥ በናያስንም፥ ኃያላኑንም፥ ወንድሙንም ሰሎሞንን አልጠራም።

11፤ ናታንም የሰሎሞንን እናት ቤርሳቤህን እንዲህ ብሎ ተናገራት። ጌታችን ዳዊት ሳያውቅ የአጊት ልጅ አዶንያስ እንደ ነገሠ አልሰማሽምን?

12፤ አሁንም ነዪ፥ የልጅሽን የሰሎሞንን ነፍስና የአንቺን ነፍስ እንድታድኝ እመክርሻለሁ።

13፤ ሄደሽ ወደ ንጉሡ ወደ ዳዊት ግቢና። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ለእኔ ለባሪያህ። ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ይቀመጣል ብለህ አልማልህልኝምን? ስለ ምንስ አዶንያስ ይነግሣል? በዪው።

14፤ እነሆ፥ አንቺ በዚያ ለንጉሥ ስትነግሪ እኔ ከአንቺ በኋላ እገባለሁ፥ ቃልሽንም አጸናለሁ።

15፤ ቤርሳቤህም ወደ ንጉሡ ወደ እልፍኝ ገባች፤ ንጉሡም እጅግ ሸምግሎ ነበር፥ ሱነማይቱም አቢሳ ታገለግለው ነበር።

16፤ ቤርሳቤህም አጐንብሳ ለንጉሡ እጅ ነሣች፤ ንጉሡም። ምን ትፈልጊያለሽ? አለ።

17፤ እርስዋም አለችው። ጌታዬ ሆይ፥ አንተ ለባሪያህ። ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ይቀመጣል ብለህ በአምላክህ በእግዚአብሔር ምለህልኛል፤

18፤ አሁንም፥ እነሆ፥ አዶንያስ መንገሡ ነው፤ አንተም ጌታዬ ንጉሥ ይህን አታውቅም፤

19፤ እርሱም ብዙ በሬዎችንና ፍሪዳዎችን በጎችንም ሠውቶአል፥ የንጉሡንም ልጆች ሁሉ፥ ካህኑንም አብያታርን፥ የሠራዊቱንም አለቃ ኢዮአብን ጠርቶአል፤ ባሪያህን ሰሎሞንን ግን አልጠራውም።

20፤ አሁንም፥ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በኋላ በጌታዬ በንጉሥ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን ትነግራቸው ዘንድ የእስራኤል ሁሉ ዓይን ይመለከትሃል።

21፤ ይህ ባይሆን፥ ጌታዬ ከአባቶችህ ጋር ባንቀላፋህ ጊዜ እኔና ልጄ ሰሎሞን እንደ ኃጢአተኞች እንቈጠራለን።

22፤ እነሆም፥ ለንጉሡ ስትናገር ነቢዩ ናታን ገባ።

23፤ ለንጉሡም። እነሆ፥ ነቢዩ ናታን መጥቶአል ብለው ነገሩት፤ እርሱም ወደ ንጉሡ ፊት በገባ ጊዜ በግምባሩ በምድር ላይ ተደፍቶ ለንጉሡ እጅ ነሣ።

24፤ ናታንም አለ። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ አንተ። ከእኔ በኋላ አዶንያስ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ላይ ይቀመጣል ብለሃልን?

25፤ እርሱ ዛሬ ወርዶ ብዙ በሬዎችንና ፍሪዳዎችን በጎችንም ሠውቶአል፥ የንጉሡንም ልጆች ሁሉ፥ የሠራዊትንም አለቃ ኢዮአብን፥ ካህኑንም አብያታርን ጠርቶአል፤ እነሆም፥ በፊቱ እየበሉና እየጠጡ። አዶንያስ ሺህ ዓመት ይንገሥ ይላሉ።

26፤ ነገር ግን እኔን ባሪያህን፥ ካህኑንም ሳዶቅን፥ የዮዳሄንም ልጅ በናያስን፥ ባሪያህንም ሰሎሞንን አልጠራም።

27፤ በውኑ ይህ ነገር ከጌታዬ ከንጉሡ የተደረገ ነውን? ለባሪያህም ከአንተ በኋላ በጌታዬ በንጉሡ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን አልነገርህምን?

28፤ ንጉሡም ዳዊት። ቤርሳቤህን ጥሩልኝ ብሎ መለሰ። ወደ ንጉሡም ገባች፥ በንጉሡም ፊት ቆመች።

29፤ ንጉሡም። ነፍሴን ከመከራ ሁሉ ያዳነኝ ሕያው እግዚአብሔርን!

30፤ በእውነት። ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በእኔም ፋንታ በዙፋኔ ላይ ይቀመጣል ብዬ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር እንደ ማልሁልሽ፥ እንዲሁ ዛሬ በእውነት አደርጋለሁ ብሎ ማለ።

31፤ ቤርሳቤህም በግምባርዋ በምድር ላይ ተደፍታ ለንጉሡ እጅ ነሣችና። ጌታዬ ንጉሥ ዳዊት ለዘላለም በሕይወት ይኑር አለች።

32፤ ንጉሡም ዳዊት። ካህኑን ሳዶቅንና ነቢዩን ናታንን የዮዳሄንም ልጅ በናያስን ጥሩልኝ አለ። ወደ ንጉሡም ፊት ገቡ።

33፤ ንጉሡም አላቸው። የጌታችሁን ባሪያዎች ይዛችሁ ሂዱ፥ ልጄንም ሰሎሞንን በበቅሎዬ ላይ አስቀምጡት፥ ወደ ግዮንም አውርዱት፤

34፤ በዚያም ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርገው ይቅቡት፤ ቀንደ መለከትም ነፍታችሁ። ሰሎሞን ሺህ ዓመት ይንገሥ በሉ።

35፤ በኋላውም ተከትላችሁ ውጡ፤ እርሱም መጥቶ በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ፥ በእኔም ፋንታ ይንገሥ፤ በእስራኤልና በይሁዳም ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ አዝዣለሁ።

36፤ የዮዳሄም ልጅ በናያስ መልሶ ለንጉሡ አለ፥ ያበጅ ያድርግ፤ የጌታዬም የንጉሥ አምላክ ይህን ይናገር።

37፤ እግዚአብሔር ከጌታዬ ከንጉሥ ጋር እንደ ነበረ እንዲሁ ከሰሎሞን ጋር ይሁን፥ ዙፋኑንም ከጌታዬ ከንጉሡ ዳዊት ዙፋን የበለጠ ያድርግ።

38፤ ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን የዮዳሄም ልጅ በናያስ ከሊታውያንና ፈሊታውያንም ወረዱ፥ ሰሎሞንንም በንጉሡ በዳዊት በቅሎ ላይ አስቀምጠው ወደ ግዮን አመጡት።

39፤ ካህኑም ሳዶቅ ከድንኳኑ የቅብዓቱን ቀንድ ወስዶ ሰሎሞንን ቀባ፤ ቀንደ መለከትም ነፉ፤ ሕዝቡም ሁሉ። ሰሎሞን ሺህ ዓመት ይንገሥ አሉ።

40፤ ሕዝቡም ሁሉ እርሱን ተከትለው ወጡ፥ ሕዝቡም ዘፈን ይዘፍኑ ነበር፥ በታላቅም ደስታ ደስ አላቸው፤ ከጩኸታቸውም የተነሣ ምድር ተናወጠች።

41፤ አዶንያስና እርሱም የጠራቸው ሁሉ መብሉና መጠጡ ተፈጽሞ ሳለ ሰሙ፤ ኢዮአብም የቀንደ መለከት ጽምፅ በሰማ ጊዜ። ይህ በከተማ ውስጥ ያለ የሽብር ድምፅ ምንድር ነው? አለ።

42፤ እርሱም ይህን ሲናገር የካህኑ የአብያታር ልጅ ዮናታን መጣ፤ አዶንያስም። አንተ መልካም ሰው ነህና፥ መልካም ታወራልናለህና ግባ አለ።

43፤ ዮናታንም ለአዶንያስ እንዲህ ብሎ መለሰ። በእውነት ጌታችን ንጉሥ ዳዊት ሰሎሞንን አነገሠው።

44፤ ንጉሡም ከእርሱ ጋር ካሁኑን ሳዶቅንና ነቢዩን ናታንን የዮዳሄንም ልጅ በናያስን ከሊታውያንንና ፈሊታውያንንም ሰደደ፥ በንጉሡም በቅሎ ላይ አስቀመጡት።

45፤ ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በግዮን ንጉሥ አድርገው ቀቡት፤ ከዚያም ደስ ብሎአቸው ወጡ፥ ከተማይቱም አስተጋባች፤ የሰማችሁትም ድምፅ ይህ ነው።

46፤ ደግሞም ሰሎሞን በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦአል።

47፤ የንጉሡም ባሪያዎች ገብተው። እግዚአብሔር የሰሎሞንን ስም ከስምህ ዙፋኑንም ከዙፋንህ የበለጠ ያድርግ ብለው ጌታችንን ንጉሡን ዳዊትን ባረኩ፤ ንጉሡም በአልጋው ላይ ሆኖ ሰገደ።

48፤ ንጉሡም ደግሞ። ዓይኔ እያየ ዛሬ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጠውን የሰጠኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን አለ።

49፤ አዶንያስም የጠራቸው ሁሉ ፈሩ፥ ተነሥተውም እያንዳንዳቸው በየመንገዳቸው ሄዱ።

50፤ አዶንያስም ሰሎሞንን ፈራ፥ ተነሥቶም ሄደ፥ የመሠዊያውንም ቀንድ ያዘ።

51፤ ለሰሎሞንም። እነሆ፥ አዶንያስ ንጉሡን ሰሎሞንን ፈርቶ። ንጉሡ ሰሎሞን ባሪያውን በሰይፍ እንዳይገድለኝ ዛሬ ይማልልኝ ብሎ የመሠዊያውን ቀንድ ይዞአል አሉት።

52፤ ሰሎሞንም። እርሱ አካሄዱን ያሳመረ እንደ ሆነ ከእርሱ አንዲት ጠጕር እንኳ በምድር ላይ አትወድቅም፤ ነገር ግን ክፋት የተገኘበት እንደ ሆነ ይሞታል አለ።

53፤ ንጉሡ ሰሎሞንም ላከ፥ ከመሠዊያውም አወረዱት፤ መጥቶም ለንጉሡ ለሰሎሞን እጅ ነሣ፥ ሰሎሞንም። ወደ ቤትህ ሂድ አለው።

መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ

ምዕራፍ 2።

1፤ ዳዊትም የሚሞትበት ቀን ቀረበ፤ ልጁንም ሰሎሞንን እንዲህ ሲል አዘዘው።

2፤ እኔ የምድሩን ሁሉ መንገድ እሄዳለሁ፤

3፤ በርታ ሰውም ሁን፤ የምታደርገውንና የምትሄድበትን ሁሉ ታከናውን ዘንድ፥ በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈ ሥርዓቱንና ትእዛዛቱን ፍርዱንና ምስክሩንም ትጠብቅ ዘንድ፥ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ፥ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ።

4፤ ይኸውም ደግሞ እግዚአብሔር ስለ እኔ። ልጆችህ መንገዳቸውን ቢጠብቁ፥ በፊቴም በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው በእውነት ቢሄዱ ከእስራኤል ዙፋን ሰው አይቈረጥብህም ብሎ የተናገረውን ቃል ያጸና ዘንድ ነው።

5፤ አንተም ደግሞ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ፥ ሁለቱን የእስራኤልን ጭፍራ አለቆች የኔር ልጅ አበኔርን የዬቴሩንም ልጅ አሜሳይን ገድሎ፥ በእኔ ላይ ያደረገውን ታውቃለህ፤ የሰልፉንም ደም በሰላም አፈሰሰ፥ በወገቡም ባለው ድግና በእግሩ ባለው ጫማ ንጹሕ ደም አኖረ።

6፤ አንተም እንደ ጥበብህ አድርግ፥ ሽበቱንም በሰላም ወደ መቃብር አታውርደው።

7፤ ከወንድምህ ከአቤሴሎም ፊት በሸሸሁ ጊዜ ቀርበውኛልና ለገለዓዳዊው ለቤርዜሊ ልጆች መልካም ቸርነት አድርግላቸው፥ በማዕድህም ከሚበሉት መካከል ይሁኑ።

8፤ እኔም ወደ መሃናይም በሄድሁ ጊዜ ብርቱ እርግማን የረገመኝ የብራቂም አገር ሰው የብንያማዊው የጌራ ልጅ ሳሚ፥ እነሆ፥ በአንተ ዘንድ ነው፤ እርሱ ግን ዮርዳኖስን በተሻገርሁ ጊዜ ሊቀበለኝ ወረደ፥ እኔም። በሰይፍ አልገድልህም ብዬ በእግዚአብሔር ምዬለታለሁ።

9፤ አንተ ግን ጥበበኛ ሰው ነህና ያለ ቅጣት አትተወው፤ የምታደርግበትንም አንተ ታውቃለህ፥ ሽበቱንም ከደም ጋር ወደ መቃብር አውርድ።

10፤ ዳዊትም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ።

11፤ ዳዊትም በእስራኤል ላይ የነገሠው ዘመን አርባ ዓመት ነበረ። በኬብሮን ሰባት ዓመት ነገሠ፤ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ።

12፤ ሰሎሞንም በአባቱ በዳዊት ዙፋን ተቀመጠ፤ መንግሥቱም እጅግ ጸና።

13፤ የአጊት ልጅ አዶንያስም ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ መጣ፤ እርስዋም። ወደ እኔ መምጣትህ በሰላም ነውን? አለች፤

14፤ እርሱም። በሰላም ነው አለ። ደግሞም። ከአንቺ ጋር ጉዳይ አለኝ አለ፤ እርስዋም። ተናገር አለች።

15፤ እርሱም። መንግሥቱ ለእኔ እንደ ነበረ፥ እስራኤልም ሁሉ ንጉሥ እሆን ዘንድ ፊታቸውን ወደ እኔ አድርገው እንደ ነበረ አንቺ ታውቂያለሽ፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆኖለታልና መንግሥቱ ከእኔ አልፎ ለወንድሜ ሆኖአል።

16፤ አሁንም አንዲት ልመና እለምንሻለሁ፤ አታሳፍሪኝ አለ። እርስዋም። ተናገር አለችው።

17፤ እርሱም። አያሳፍርሽምና ሱነማይቱን አቢሳን ይድርልኝ ዘንድ ለንጉሡ ለሰሎሞን እንድትነግሪው እለምንሻለሁ አለ።

18፤ ቤርሳቤህም። መልካም ነው፥ ስለ አንተ ለንጉሡ እነግረዋለሁ አለች።

19፤ ቤርሳቤህም የአዶንያስን ነገር ትነግረው ዘንድ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ገባች፤ ንጉሡም ሊቀበላት ተነሣ ሳማትም፥ በዙፋኑም ተቀመጠ፤ ለንጉሡም እናት ወንበር አስመጣላት፥ በቀኙም ተቀመጠች።

20፤ እርስዋም። አንዲት ታናሽ ልመና እለምንሃለሁ፤ አታሳፍረኝ አለች። ንጉሡም። እናቴ ሆይ፥ አላሳፍርሽምና ለምኝ አላት።

21፤ እርስዋም። ሱነማይቱ አቢሳ ለወንድምህ ለአዶንያስ ትዳርለት አለች።

22፤ ንጉሡም ሰሎሞን ለእናቱ መልሶ። ሱነማይቱን አቢሳን ለአዶንያስ ለምን ትለምኝለታለሽ? ታላቅ ወንድሜ ነውና መንግሥትን ደግሞ ለምኚለት፤ ካህኑም አብያታርና የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ ደግሞ ከእርሱ ጋር ናቸው አላት።

23፤ ንጉሡም ሰሎሞን። አዶንያስ ይህን ቃል በሕይወቱ ላይ አለመናገሩ እንደ ሆነ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፥ ይህንም ይጨምርብኝ።

24፤ አሁንም ያጸናኝ፥ በአባቴም በዳዊት ዙፋን ላይ ያስቀመጠኝ፥ እንደ ተናገረውም ቤትን የሠራልኝ ሕያው እግዚአብሔርን! ዛሬ አዶንያስ ፈጽሞ ይገደላል ብሎ በእግዚአብሔር ማለ።

25፤ ንጉሡም ሰሎሞን የዮዳሄን ልጅ በናያስን ላከ፤ እርሱም ወደቀበት፥ ሞተም።

26፤ ንጉሡም ካህኑን አብያታርን። አንተ ዛሬ የሞት ሰው ነበርህ፤ ነገር ግን የአምላክን የእግዚአብሔርን ታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ስለ ተሸከምህ፥ አባቴም የተቀበለውን መከራ ሁሉ አንተ ስለ ተቀበልህ አልገድልህምና በዓናቶት ወዳለው ወደ እርሻህ ሂድ አለው።

27፤ በሴሎም በዔሊ ቤት ላይ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ ሰሎሞን አብያታርን ከእግዚአብሔር ክህነት አወጣው።

28፤ ለኢዮአብም ወሬ ደረሰለት፤ ኢዮአብም አቤሴሎምን አልተከተለም ነበር እንጂ አዶንያስን ተከትሎ ነበር። ኢዮአብም ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ የመሠዊያውን ቀንድ ያዘ።

29፤ ንጉሡም ሰሎሞን ኢዮአብ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ መሠዊያውን እንደ ያዘ ሰማ፤ ሰሎሞንም የዮዳሄን ልጅ በናያስን፥ ሂድ ውደቅበት ብሎ አዘዘው።

30፤ በናያስም ወደ እግዚአብሔር ድንኳን መጥቶ። ንጉሡ። ውጣ ይልሃል አለው፤ እርሱም። በዚህ እሞታለሁ እንጂ አልወጣም አለ። በናያስም። ኢዮአብ የተናገረው ቃል የመለሰልኝም እንዲህ ነው ብሎ ወደ ንጉሡ ወሬ አመጣ።

31፤ ንጉሡም አለው። እንደ ነገረህ አድርግ፤ ኢዮአብም በከንቱ ያፈሰሰውን ደም ከእኔና ከአባቴ ቤት ታርቅ ዘንድ ገድለህ ቅበረው።

32፤ አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ከእርሱ የሚሻሉትን ሁለቱን ጻድቃን ሰዎች፥ የእስራኤልን ሠራዊት አለቃ የኔርን ልጅ አበኔርን፥ የይሁዳንም ሠራዊት አለቃ የዬቴርን ልጅ አሜሳይን፥ በሰይፍ ገድሎአልና እግዚአብሔር ደሙን በራሱ ላይ ይመልሰው።

33፤ ደማቸውም በኢዮአብ ራስና በዘሩ ራስ ላይ ለዘላለም ይመለስ፤ ለዳዊት ግን ለዘሩና ለቤቱ ለዙፋኑም የእግዚአብሔር ሰላም ለዘላለም ይሁን።

34፤ የዮዳሄም ልጅ በናያስ ወጥቶ ወደቀበት ገደለውም፤ በምድረ በዳም ባለው በቤቱ ተቀበረ።

35፤ ንጉሡም በእርሱ ፋንታ የዮዳሄን ልጅ በናያስን የሠራዊቱ አለቃ አደረገ፤ በአብያታርም ፋንታ ካህኑን ሳዶቅን አደረገ።

36፤ ንጉሡም ልኮ ሳሚን አስጠራውና። በኢየሩሳሌም ቤት ሠርተህ ተቀመጥ፥ ወዲህና ወዲያም አትውጣ።

37፤ በወጣህበትም ቀን፥ የቄድሮንንም ፈፋ በተሻገርህበት ቀን ፈጽመህ እንድትሞት እወቅ፤ ደምህ በራስህ ላይ ይሆናል አለው።

38፤ ሳሚም ንጉሡን። ነገሩ መልካም ነው፤ ጌታዬ ንጉሥ እንደ ተናገረ ባሪያህ እንዲሁ ያደርጋል አለው፤ ሳሚም በኢየሩሳሌም ብዙ ቀን ተቀመጠ።

39፤ ከሦስት ዓመትም በኋላ ከሳሚ ባሪያዎች ሁለቱ ወደ ጌት ንጉሥ ወደ መዓካ ልጅ ወደ አንኩስ ኰበለሉ፤ ሳሚንም። እነሆ፥ ባሪያዎችህ በጌት ናቸው ብለው ነገሩት።

40፤ ሳሚም ተነሣ፥ አህያውንም ጭኖ ባሪያዎቹን ይሻ ዘንድ ወደ ጌት ወደ አንኩስ ዘንድ ሄደ፤ ሳሚም ሄዶ ባሪያዎቹን ከጌት አመጣ።

41፤ ሰሎሞንም ሳሚ ከኢየሩሳሌም ወደ ጌት ሄዶ እንደ ተመለሰ ሰማ።

42፤ ንጉሡም ልኮ ሳሚን አስጠራና። ወዲህና ወዲያ ለመሄድ በወጣህ ቀን ፈጽመህ እንድትሞት እወቅ ብዬ በእግዚአብሔር አላስማልሁህምን? ወይስ አላስመሰከርሁብህምን? አንተም። ቃሉ መልካም ነው፥ ሰምቻለሁ አልኸኝ።

43፤ የእግዚአብሔርን መሐላ እኔስ ያዘዝሁህን ትእዛዝ ስለ ምን አልጠበቅህም? አለው።

44፤ ንጉሡም ደግሞ ሳሚን። አንተ በአባቴ በዳዊት ላይ የሠራኸውን ልብህም ያሰበውን ክፋት ሁሉ ታውቃለህ፤ እግዚአብሔርም ክፋትህን በራስህ ላይ ይመልሳል።

45፤ ንጉሡ ሰሎሞን ግን የተባረከ ይሆናል፥ የዳዊትም ዙፋን በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም ይጸናል አለው።

46፤ ንጉሡም የዮዳሄን ልጅ በናያስን አዘዘው፥ ወጥቶም ወደቀበት፥ ሞተም። መንግሥትም በሰሎሞን እጅ ጸና። a

መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ

ምዕራፍ 3።

1፤ ሰሎሞንም ለግብጽ ንጉሥ ለፈርዖን አማች ሆነ፤ የፈርዖንን ልጅ አገባ፥ ቤቱንና የእግዚአብሔርንም ቤት በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ያለውን ቅጥር ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ ወደ ዳዊት ከተማ አመጣት።

2፤ እስከዚያም ቀን ድረስ ለእግዚአብሔር ስም መቅደስ አልተሠራም ነበርና ሕዝቡ በኮረብታ ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋ ነበር።

3፤ ሰሎሞንም እግዚአብሔርን ይወድድ ነበር፥ በአባቱም በዳዊት ሥርዓት ይሄድ ነበር፤ ብቻ በኮረብታ መስገጃ ይሠዋና ያጥን ነበር።

4፤ ገባዖን ዋና የኮረብታ መስገጃ ነበረችና ንጉሡ ይሠዋ ዘንድ ወደዚያ ሄደ፤ ሰሎሞንም በዚያ መሠዊያ ላይ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ።

5፤ እግዚአብሔርም በገባዖን ለሰሎሞን በሌሊት በሕልም ተገለጠለት፤ እግዚአብሔርም። ምን እንድሰጥህ ለምን አለ።

6፤ ሰሎሞንም አለ። እርሱ በፊትህ በእውነትና በጽድቅ በልብም ቅንነት ከአንተ ጋር እንደ ሄደ፥ ከባሪያህ ከአባቴ ከዳዊት ጋር ታላቅ ቸርነት አድርገሃል፤ ዛሬ እንደ ሆነም በዙፋኑ ላይ የሚቀመጥ ልጅ ሰጥተህ ታላቁን ቸርነትህን አቆይተህለታል።

7፤ አሁንም፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ እኔን ባሪያህን በአባቴ በዳዊት ፋንታ አንግሠኸኛል፤ እኔም መውጫንና መግቢያን የማላውቅ ታናሽ ብላቴና ነኝ።

8፤ ባሪያህም ያለው አንተ በመረጥኸው ሕዝብህ ስለ ብዛቱም ይቈጠርና ይመጠን ዘንድ በማይቻል በታላቅ ሕዝብ መካከል ነው።

9፤ ስለዚህም በሕዝብህ ላይ መፍረድ ይችል ዘንድ፥ መልካሙንና ክፉውንም ይለይ ዘንድ ለባሪያህ አስተዋይ ልቡና ስጠው፤ አለዚያማ በዚህ በታላቅ ሕዝብህ ላይ ይፈድ ዘንድ ማን ይችላል?

10፤ ሰሎሞንም ይህን ነገር ስለ ለመነ፥ ነገሩ እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው።

11፤ እግዚአብሔርም አለው። ፍርድን ትለይ ዘንድ ለራስህ ማስተዋልን ለመንህ እንጂ ለራስህ ብዙ ዘመናትን ባለጠግነትንም የጠላቶችህንም ነፍስ ሳትለምን ይህን ነገር ለምነሃልና እነሆ፥

12፤ እኔ እንደ ቃል አድርጌልሃለሁ፤ እነሆ፥ ማንም የሚመስልህ ከአንተ በፊት እንደሌለ ከአንተም በኋላ እንዳይነሣ አድርጌ ጥበበኛና አስተዋይ ልቡና ሰጥቼሃለሁ።

13፤ ደግሞም ከነገሥታት የሚመስልህ ማንም እንዳይኖር ያልለመንኸውን ባለጠግነትና ክብር ሰጥቼሃለሁ።

14፤ አባትህም ዳዊት እንደ ሄደ፥ ሥርዓቴንና ትእዛዜን ትጠብቅ ዘንድ በመንገዴ የሄድህ እንደ ሆነ፥ ዕድሜህን አረዝመዋለሁ።

15፤ ሰሎሞንም ነቃ፥ እነሆም፥ ሕልም ነበረ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም መጥቶ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ቆመ፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አሳረገ፥ የደኅንነትንም መሥዋዕት አቀረበ፥ ለባሪያዎቹም ሁሉ ግብዣ አደረገ።

16፤ በዚያን ጊዜም ሁለት ጋለሞቶች ሴቶች ወደ ንጉሡ መጥተው በፊቱ ቆሙ።

17፤ አንደኛይቱም ሴት አለች። ጌታዬ ሆይ፥ እኔና ይህች ሴት በአንድ ቤት እንኖራለን፤ እኔም ከእርስዋ ጋር በቤት ሳለሁ ወለድሁ።

18፤ እኔ ከወለድሁ ከሦስት ቀን በኋላ ይህች ሴት ደግሞ ወለደች፤ እኛ በቤት ውስጥ አብረን ነበርን፥ ከሁለታችንም በቀር ማንም በቤት ውስጥ አልነበረም።

19፤ እርስዋም በላዩ ስለ ተኛችበት የዚህች ሴት ልጅ በሌሊት ሞተ።

20፤ እርስዋም በእኩለ ሌሊት ተነሥታ፥ እኔ ባሪያህ ተኝቼ ሳለሁ፥ ልጄን ከአጠገቤ ወሰደች፥ በብብትዋም አደረገችው፥ የሞተውንም ልጅዋን በእኔ ብብት አደረገች።

21፤ ልጄንም አጠባ ዘንድ በማለዳ ብነሣ፥ እነሆ፥ ሞቶ ነበር፤ ነገር ግን ብርሃን በሆነ ጊዜ ተመለከትሁት፥ እነሆም፥ የወለድሁት ልጄ አልነበረም።

22፤ ሁለተኛይቱም ሴት። ደኅነኛው የኔ ልጅ ነው፥ የሞተውም የአንቺ ልጅ ነው እንጂ አንቺ እንደምትዪው አይደለም አለች። ይህችም። የሞተው የአንቺ ልጅ ነው፥ ደኅነኛውም የእኔ ልጅ ነው አለች፤ እንዲሁም በንጉሡ ፊት ይነጋገሩ ነበር።

23፤ በዚያን ጊዜም ንጉሡ። ይህች። ደኅነኛው የእኔ ልጅ ነው፥ የሞተውም የአንቺ ልጅ ነው ትላለች፤ ያችኛይቱም። አይደለም፥ የሞተው የአንቺ ልጅ ነው ደኅነኛውም የእኔ ልጅ ነው ትላለች አለ።

24፤ ንጉሡም። ሰይፍ አምጡልኝ አለ፤ ሰይፍም ይዘው ወደ ንጉሡ ፊት መጡ።

25፤ ንጉሡም። ደኅነኛውን ሕፃን ለሁለት ከፍላችሁ ለአንዲቱ አንዱን ክፍል፥ ለሁለተኛይቱም ሁለተኛውን ክፍል ስጡ አለ።

26፤ ደኅነኛውም የነበራት ሴት አንጀትዋ ስለ ልጅዋ ናፍቆአልና። ጌታዬ ሆይ፥ ደኀነኛውን ለእርስዋ ስጣት እንጂ አትግደል ብላ ለንጉሡ ተናገረች። ያችኛይቱ ግን። ይከፈል እንጂ ለእኔም ለአንቺም አይሁን አለች።

27፤ ንጉሡም መልሶ። ይህችኛይቱ እናቱ ናትና ደኅነኛውን ሕፃን ለእርስዋ ስጡአት እንጂ አትግደሉት አለ።

28፤ ንጉሡም የፈረደውን ፍርድ እስራኤል ሁሉ ሰሙ፤ ፍርድን ለማድረግ የእግዚአብሔር ጥበብ እንደ ነበረበት አይተዋልና ንጉሡን ፈሩ።

መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ

ምዕራፍ 4።

1፤ ንጉሡም ሰሎሞን በእስራኤል ሁሉ ላይ ነግሦ ነበር።

2፤ የነበሩትም አለቆች እነዚህ ናቸው፤ የሳዶቅ ልጅ ካህኑ ዓዛርያስ፥

3፤ ጸሐፊዎቹም የሴባ ልጆች ኤልያፍና አኪያ፥ ታሪክ ጸሐፊም የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ፥

4፤ የዮዳሄም ልጅ በናያስ የሠራዊት አለቃ ነበረ፤ ሳዶቅና አብያታርም ካህናት ነበሩ፤

5፤ የናታንም ልጅ ዓዛርያስ የሹሞች አለቃ ነበረ፤ የናታንም ልጅ ዛቡድ የንጉሡ አማካሪና ወዳጅ ነበረ፤

6፤ አሒሳርም የቤት አዛዥ፥ የዓብዳም ልጅ አዶኒራም አስገባሪ ነበረ።

7፤ ለንጉሡና ለቤተ ሰቡም ቀለብ የሚሰጡ በእስራኤል ሁሉ ላይ አሥራ ሁለት ሹሞች ለሰሎሞን ነበሩት። ከዓመቱ ውስጥ አንዱን ወር እያንዳንዳቸው ይቀልቡ ነበር።

8፤ ስማቸውም ይህ ነበረ፤ በተራራማው አገር በኤፍሬም የሑር ልጅ፤

9፤ በማቃጽና በሸዓልቢም በቤትሳሚስና በኤሎንቤትሐናን የዴቀር ልጅ፤

10፤ በአሩቦት የሔሴድ ልጅ፥ ለእርሱም ሰኰትና የኦፌር አገር ሁሉ ነበረ፤

11፤ በዶር አገር ዳርቻ ሁሉ የአሚናዳብ ልጅ፥ እርሱም የሰሎሞንን ልጅ ጣፈትን አግብቶ ነበር፤

12፤ ከቤትሳን ጀምሮ እስከ አቤልምሖላና እስከ ዮቅምዓም ማዶ ድረስ በታዕናክና በመጊዶ በጸርታንም አጠገብ በኢይዝራኤል በታች ባለው በቤትሳን ሁሉ የአሒሉድ ልጅ በዓና ነበረ፤

13፤ በሬማት ዘገለዓድ የጌበር ልጅ ነበረ፥ ለእርሱም በገለዓድ ያሉት የምናሴ ልጅ የኢያዕር መንደሮች ነበሩ፤ ለእርሱም ደግሞ በባሳን በአርጎብ ዳርቻ ያሉት ቅጥርና የናስ መወረወሪያዎች የነበረባቸው ስድሳ ታላላቅ ከተሞች ነበሩበት፤

14፤ በመሃናይም የዒዶ ልጅ አሒናዳብ፤

15፤ በንፍታሌም አኪማአስ ነበረ፥ እርሱም የሰሎሞንን ልጅ ባስማትን አግብቶ ነበር፤

16፤ በአሴርና በበዓሎት የኩሲ ልጅ በዓና፤

17፤ በይሳኮር የፋሩዋ ልጅ ኢዮሣፍጥ፤

18፤ በብንያም የኤላ ልጅ ሳሚ፤

19፤ በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎንና በባሳን ንጉሥ በዐግ አገር፥ በገለዓድ አገር፥ የኡሪ ልጅ ጌበር ነበረ፤ በዚያችም ምድር ላይ እርሱ ብቻውን ሹም ነበረ።

20፤ ይሁዳና እስራኤልም እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ ነበሩ፤ በልተውም ጠጥተውም ደስ ብሎአቸው ነበር።

21፤ ሰሎሞንም ከወንዙ ጀምሮ እስከ ግብጽ ዳርቻ እስከ ፍልስጥኤም ድረስ በመንግሥታት ሁሉ ላይ ነግሦ ነበር፤ ግብርም ያመጡለት ነበር፥ በዕድሜውም ሙሉ ለሰሎሞን ይገዙ ነበር።

22፤ ለሰሎሞንም ለቀን ለቀኑ ቀለብ የሚሆን ሠላሳ ኮር መልካም ዱቄትና ስድሳ ኮር መናኛ ድቄት፥

23፤ ከዋላና ከሚዳቋ ከበረሀ ፍየልና ከሰቡ ወፎች በቀር አሥር ፍሪዳዎች ሀያም የተሰማሩ በሬዎች አንድ መቶም በጎች ነበረ።

24፤ ከወንዙ ወዲህ ባሉት ነገሥታት ሁሉ ከወንዙም ወዲህ ባለው አገር ሁሉ ላይ ከቲፍሳ ጀምሮ እስከ ጋዛ ድረስ ነግሦ ነበር፤ በዙሪያውም ባለው በሁሉ ወገን ሰላም ሆኖለት ነበር።

25፤ በሰሎሞንም ዘመን ሁሉ ይሁዳና እስራኤል ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ተዘልሎ ይቀመጥ ነበር።

26፤ ለሰሎሞንም በአርባ ሺህ ጋጥ የሚገቡ የሰረገላ ፈረሶች አሥራ ሁለትም ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት።

27፤ እነዚያም ሹሞች እያንዳንዱ በየወሩ ንጉሡን ሰሎሞንንና ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ማዕድ የሚቀርቡትን ሁሉ ይቀልቡ ነበር፤ ምንም አያጎድሉም ነበር።

28፤ እያንዳንዱም እንደ ደንቡ ለፈረሶቹና ለሰጋር በቅሎች ገብስና ጭድ ወደ ስፍራቸው ያመጡ ነበር።

29፤ እግዚአብሔርም ለሰሎሞን እጅግ ብዙ ጥበብና ማስተዋል በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋት ሰጠው።

30፤ የሰሎሞንም ጥበብ በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ጥበብና ከግብጽ ጥበብ ሁሉ በለጠ።

31፤ ከሰውም ሁሉ ይልቅ ከኢይዝራኤላዊው ከኤታንና ከማሖል ልጆች ከሄማንና ከከልቀድ ከደራልም ይልቅ ጥበበኛ ነበረ። በዙሪያውም ባሉ አሕዛብ ሁሉ ዝናው ወጣ።

32፤ እርሱም ሦስት ሺህ ምሳሌዎች ተናገረ፤ መኃልዩም ሺህ አምስት ነበረ።

33፤ ስለ ዛፍም ከሊባኖስ ዝግባ ጀምሮ በቅጥር ግንብ ላይ እስከሚበቅለው እስከ ሂሶጵ ድረስ ይናገር ነበር፤ ደግሞም ስለ አውሬዎችና ስለ ወፎች ሰለተንቀሳቃሾችና ስለ ዓሣዎች ይናገር ነበር።

34፤ ከአሕዛብም ሁሉ፥ ጥበቡንም ሰምተው ከነበሩ ከምድር ነገሥታት ሁሉ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ሰዎች ይመጡ ነበር። a

መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ

ምዕራፍ 5።

1፤ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ለዳዊት በዘመኑ ሁሉ ወዳጅ ስለ ነበረ፥ ሰሎሞን በአባቱ ፋንታ ንጉሥ ለመሆን እንደ ተቀባ ሰምቶ ባሪያዎቹን ወደ ሰሎሞን ሰደደ።

2፤ ሰሎሞንም ወደ ኪራም እንዲህ ብሎ ላከ።

3፤ እግዚአብሔር ከእግሩ በታች እስኪጥልለት ድረስ በዙሪያው ስለ ነበረ ሰልፍ አባቴ ዳዊት የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት እንዳልቻለ አንተ ታውቃለህ።

4፤ አሁንም አምላኬ እግዚአብሔር በዙሪያዬ ካሉት ዕረፍት ሰጥቶኛል፤ ጠላትም ክፉም ነገር የለብኝም።

5፤ እነሆም፥ እግዚአብሔር ለአባቴ ለዳዊት። በአንተ ፋንታ በዙፋንህ ላይ የማስቀምጠው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል ብሎ እንደ ነገረው፥ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤት እሠራ ዘንድ አስባለሁ።

6፤ አሁንም ከወገኔ እንደ ሲዶናውያን እንጨት መቈረጥ የሚያውቅ እንደሌለ ታውቃለህና የዝግባ ዛፍ ከሊባኖስ ይቈርጡልኝ ዘንድ ባሪያዎችህን እዘዝ፤ ባሪያዎቼም ከባሪያዎችህ ጋር ይሁኑ፤ የባሪያዎችህንም ዋጋ እንደ ተናገርኸው ሁሉ እሰጥሃለሁ።

7፤ ኪራምም የሰሎሞንን ቃል ሰምቶ እጅግ ደስ አለውና። በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ ጥበበኛ ልጅ ለዳዊት የሰጠ እግዚአብሔር ዛሬ ይመስገን አለ።

8፤ ኪራምም። የላክህብኝን ሁሉ ሰማሁ፤ ስለ ዝግባውና ስለ ጥዱ እንጨት ፈቃድህን ሁሉ አደርጋለሁ።

9፤ ባሪያዎቼ ከሊባኖስ ወደ ባሕር ይጐትቱታል፤ እኔም በታንኳ አድርጌ በባሕር ላይ እያንሳፈፍሁ አንተ እስከ ወሰንኸው ስፍራ ድረስ አደርስልሃለሁ፥ በዚያም እፈታዋለሁ፥ አንተም ከዚያ ታስወስደዋለህ፤ አንተም ፈቃዴን ታደርጋለህ፤ ለቤቴም ቀለብ የሚሆነውን ትሰጠኛለህ ብሎ ወደ ሰሎሞን ላከ።

10፤ እንዲሁም ኪራም የዝግባውንና የጥዱን እንጨት እንደሚሻው ያህል ሁሉ ለሰሎሞን ይሰጠው ነበር።

11፤ ሰሎሞንም ለኪራም ስለ ቤቱ ቀለብ ሀያ ሺ የቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ ሀያ ኮርም ጥሩ ዘይት ይሰጠው ነበር፤ ሰሎሞንም ለኪራም በየዓመቱ ይህን ይሰጥ ነበር።

12፤ እግዚአብሔርም እንደ ነገረው ለሰሎሞን ጥበብን ሰጠው፤ በኪራምና በሰሎሞንም መካከል ሰላም ነበረ፤ ሁለቱም ቃል ኪዳን ተጋቡ።

13፤ ሰሎሞንም ከእስራኤል ሁሉ ገባሮቹን መርጦ አወጣ፤ የገባሮቹም ቍጥር ሠላሳ ሺህ ሰዎች ነበረ።

14፤ በየወሩም እያከታተለ ወደ ሊባኖስ አሥር አሥር ሺህ ይሰድድ ነበር፤ አንድ ወርም በሊባኖስ ሁለት ወርም በቤታቸው ይቀመጡ ነበር። አዶኒራምም አስገባሪ ነበረ።

15፤ ሰሎሞንም ሰባ ሺህ ተሸካሚዎች፥ ሰማንያ ሺህም በተራራው ላይ የሚጠርቡ ጠራቢዎች ነበሩት።

16፤ ይኸውም በሠራተኛው ሕዝብ ላይ ከተሾሙት ከሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎች ሌላ ነው።

17፤ ንጉሡም ታላላቅ ምርጥ ምርጥ ድንጋዮችን ይቈፍሩና ይጠርቡ ዘንድ ለቤቱም መሠረት ይረበርቡት ዘንድ አዘዘ።

18፤ የሰሎሞንና የኪራምም አናጢዎች ጌባላውያንም ወቀሩአቸው፥ ቤቱንም ለመሥራት እንጨቱንና ድንጋዮቹን አዘጋጁ።

መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ

ምዕራፍ 6።

1፤ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር ከወጡ አራት መቶ ሰማንያ ዓመት በሆነ ጊዜ፥ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ዚፍ በሚባለው በሁለተኛው ወር የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመረ።

2፤ ንጉሡ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር የሠራው ቤት ርዝመቱ ስድሳ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ፥ ቁመቱም ሠላሳ ክንድ ነበረ።

3፤ በመቅደሱም ፊት ወለል ነበረ፤ ርዝመቱም እንደ መቅደሱ ወርድ ሀያ ክንድ፥ ወርዱም ከቤቱ ወደፊት አሥር ክንድ ነበረ።

4፤ ለቤቱም በዓይነ ርግብ የተዘጉ መስኮቶች አደረገ።

5፤ በቤቱም ግንብ ዙሪያ፥ በመቅደሱና በቅድስተ ቅዱሳኑ ግንብ ዙሪያ፥ ደርብ ሠራ፥ በዙሪያውም ጓዳዎች አደረገ።

6፤ የታችኛውም ደርብ ወርዱ አምስት ክንድ፥ የመካከለኛው ደርብ ወርዱ ስድስት ክንድ፥ የሦስተኛውም ደርብ ወርዱ ሰባት ክንድ ነበረ። ሰረገሎቹ በቤቱ ግንብ ውስጥ እንዳይገቡ ከቤቱ ግንብ ውጭ ዓረፍቶች አደረገ።

7፤ ቤቱም በተሠራ ጊዜ ፈጽመው በተወቀሩ ድንጋዮች ተሠራ፤ በተሠራም ጊዜ መራጃና መጥረቢያ የብረትም ዕቃ ሁሉ በቤቱ ውስጥ አልተሰማም።

8፤ የታችኛውም ደርብ ጓዳዎች በር በቤቱ ቀኝ አጠገብ ነበረ። ከዚያም ወደ መካከለኛው ደርብ፥ ከመካከለኛውም ወደ ሦስተኛው ደርብ በመውጫ ያስወጣ ነበር።

9፤ ቤቱንም ሠርቶ ፈጸመው፤ በዝግባው ሰረገሎችና ሳንቃዎች ከደነው።

10፤ በቤቱም ሁሉ ዙሪያ ቁመታቸው አምስት አምስት ክንድ የሆነ ደርቦች ሠራ፤ ከቤቱም ጋር በዝግባ እንጨት አጋጠማቸው።

11፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ሰሎሞን መጣ እንዲህ ሲል።

12፤ ስለዚህ ስለምትሠራው ቤት በሥርዓቴ ብትሄድ፥ ፍርዴንም ብታደርግ፥ ትመላለስበትም ዘንድ ትእዛዜን ሁሉ ብትጠብቅ፥ ለአባትህ ለዳዊት የነገርሁትን ቃል ከአንተ ጋር አጸናለሁ።

13፤ በእስራኤልም ልጆች መካከል እኖራለሁ፥ ሕዝቤንም እስራኤልን አልጥልም።

14፤ ሰሎሞንም ቤቱን ሠራው፥ ፈጸመውም።

15፤ የቤቱንም ግንብ ውስጡን በዝግባ ሳንቃ ለበጠ፤ ከቤቱም መሠረት ጀምሮ እስከ ጣራው ድረስ ውስጡን በእንጨት ለበጠው፤ ደግሞም የቤቱን ወለል በጥድ እንጨት ከደነው።

16፤ በቤቱ ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳን ይሆን ዘንድ ኋለኛውን ሀያውን ክንድ በዝግባ እንጨት ጋረደው።

17፤ በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ያለውም መቅደስ ርዝመቱ አርባ ክንድ ነበረ።

18፤ የቤቱንም ውስጥ በተጐበጐበና በፈነዳ አበባ በተቀረጸ ዝግባ ለበጠው፤ ሁሉም ዝግባ ነበረ፤ ድንጋዩም አልታየም ነበር።

19፤ በዚያም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ያኖር ዘንድ በቤቱ ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳኑን አበጀ።

20፤ የቅድስተ ቅዱሳንም ርዝመት ሀያ ክንድ፥ ስፋቱም ሀያ ክንድ፥ ቁመቱም ሀያ ክንድ ነበረ፤ በጥሩ ወርቅም ለበጠው።

21፤ በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት ከዝግባ የተሠራ መሠዊያ አደረገ፤ በጥሩ ወርቅም ለበጠው።

22፤ ቤቱንም ሁሉ ፈጽሞ በወርቅ ለበጠው፤ በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት የነበረውን መሠዊያ ሁሉ በወርቅ ለበጠው።

23፤ በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ ቁመታቸው አሥር ክንድ የሆነ ከወይራ እንጨት ሁለት ኪሩቤል ሠራ።

24፤ የኪሩብም አንደኛው ክንፍ አምስት ክንድ፥ የኪሩብም ሁለተኛው ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፤ ከአንደኛው ክንፍ ጫፍ ጀምሮ እስክ ሁለተኛው ክንፍ ጫፍ ድረስ አሥር ክንድ ነበረ።

25፤ ሁለተኛውም ኪሩብ አሥር ክንድ ነበረ፤ ሁለቱም ኪሩቤል አንድ ልክና አንድ መልክ ነበረ።

26፤ የአንዱ ኪሩብ ቁመት አሥር ክንድ ነበረ፥ የሁለተኛውም ኪሩብ እንዲሁ ነበረ።

27፤ ኪሩቤልንም በውስጠኛው ቤት አኖራቸው፤ የኪሩቤልም ክንፎቻቸው ተዘርግተው ነበር፤ የአንዱም ኪሩብ ክንፍ አንደኛውን ግንብ ይነካ ነበር፥ የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ ሁለተኛውን ግንብ ይነካ ነበር፤ የሁለቱም ክንፎች በቤቱ መካከል እርስ በርሳቸው ይነካኩ ነበር።

28፤ ኪሩቤልንም በወርቅ ለበጣቸው።

29፤ በቤቱም ግንብ ሁሉ ዙሪያ በውስጥና በውጭ የኪሩቤልና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸ።

30፤ የቤቱንም ወለል በውስጥና በውጭ በወርቅ ለበጠ።

31፤ ለቅዱስተ ቅዱሳኑም መግቢያ ከወይራ እንጨት ደጆች ሠራ፤ መድረኩንና መቃኖቹን ደፉንም አምስት ማዕዘን አደረገ።

32፤ ሁለቱንም ደጆች ከወይራ እንጨት ሠራ፤ የኪሩቤልንና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸባቸው፥ በወርቅም ለበጣቸው፤ ኪሩቤልናና የዘንባባውን ዛፍ በወርቅ ለበጣቸው።

33፤ እንዲሁም ለመቅደሱ መግቢያ ከወይራ እንጨት አራት ማዕዘን መቃን አደረገ።

34፤ ሁለቱንም ደጆች ከጥድ እንጨት ሠራ፤ አንዱ ደጅ በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ፥ ሁለተኛውም ደጅ በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ።

35፤ የኪሩቤልንና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸባቸው፤ በተቀረጸውም ሥራ ላይ በወርቅ ለበጣቸው።

36፤ የውስጠኛውንም አደባባይ ቅጥር ሦስቱን ተራ በተጠረበ ድንጋይ፥ አንዱንም ተራ በዝግባ ሳንቃ ሠራው።

37፤ በአራተኛው ዓመት ዚፍ በሚባል ወር የእግዚአብሔር ቤት ተመሠረተ።

38፤ በአሥራ አንደኛውም ዓመት ቡል በሚባል በስምንተኛው ወር ቤቱ እንደ ክፍሎቹና እንደ ሥርዓቱ ሁሉ ተጨረሰ። በሰባትም ዓመት ውስጥ ሠራው። a

መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ

ምዕራፍ 7።

1፤ ሰሎሞንም የራሱን ቤት በአሥራ ሦስት ዓመት ሠራ፥ የቤቱንም ሥራ ሁሉ ጨረሰ።

2፤ የሊባኖስ ዱር ቤት የሚባል ቤትን ሠራ፤ ርዝመቱንም መቶ ክንድ፥ ስፋቱንም አምሳ ክንድ፥ ቁመቱንም ሠላሳ ክንድ አደረገ፤ የዝግባም እንጨት በሦስት ተራ በተሠሩ አዕማድ ላይ ቆሞ ነበር፤ በአዕማዱም ላይ የዝግባ እንጨት አግዳሚ ሰረገሎች ነበሩ።

3፤ በአዕማዱም ላይ በነበሩ አግዳሚዎች ቤቱ በዝግባ ሳንቃ ተሸፍኖ ነበር፤ አዕማዱም በአንዱ ተራ አሥራ አምስት፥ በአንዱ ተራ አሥራ አምስት እየሆኑ አርባ አምስት ነበሩ።

4፤ መስኮቶቹም በሦስት ተራ ነበሩ፥ መስኮቶቹም ፊት ለፊት ይተያዩ ነበር።

5፤ ደጆቹና መስኮቶቹም ሁሉ አራት ማዕዘን ነበሩ፤ መስኮቶቹም በሦስት ተራ ሆነው ፊት ለፊት ይተያዩ ነበር።

6፤ አዕማዱም ያሉበቱን ቤት ሠራ፤ ርዝመቱም አምሳ ክንድ፥ ስፋቱም ሠላሳ ክንድ ነበረ፤ በእርሱም ፊት ደግሞ አዕማድና መድረክ ያሉበት ወለል ነበረ።

7፤ ደግሞም የሚፈርድበት ዙፋን ያለበትን የፍርድ ቤት አደረገ። ከወለሉም አንሥቶ እስከ ጣራው ድረስ በዝግባ እንጨት ተሸፍኖ ነበር።

8፤ ከፍርድ ሰቀላ ወደ ውስጥ፥ በሌላውም አደባባይ ውስጥ የነበረውን መኖሪያ ቤት እንዲሁ ሠራ። እንደዚሁም ያለ ቤት ሰሎሞን ላገባት ለፈርዖን ልጅ ቤት ሠራ።

9፤ እነዚህም ሁሉ ከመሠረቱ ጀምሮ እስከ ጕልላቱ ድረስ በጥሩ በተጠረበና በውስጥና በውጭ በልክ በተከረከመ ድንጋይ ተሠርተው ነበር፤ በውጭውም እስከ ታላቁ አደባባይ ድረስ እንዲሁ ነበረ።

10፤ መሠረቱም አሥር ወይም ስምንት ክንድ በሆነ በጥሩና በታላቅ ድንጋይ ተሠርቶ ነበር።

11፤ በላዩም ልክ ሆኖ የተከረከመ ጥሩ ድንጋይና የዝግባ ሳንቃ ነበረ።

12፤ በታላቁም አደባባይ ዙሪያ የነበረው ቅጥር እንደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ውስጠኛው አደባባይ ቅጥርና እንደ ቤቱ ወለል ሦስቱ ተራ በተጠረበ ድንጋይ አንዱም ተራ በዝግባ ሳንቃ ተሠርቶ ነበር።

13፤ ንጉሡም ሰሎሞን ልኮ ኪራምን ከጢሮስ አስመጣ።

14፤ እርሱም ከንፍታሌም ወገን የነበረች የባል አልባ ሴት ልጅ ነበረ፥ አባቱም የጢሮስ ሰው ናስ ሠራተኛ ነበረ፤ የናስንም ሥራ ሁሉ ይሠራ ዘንድ በጥበብና በማስተዋል በብልሃትም ተሞልቶ ነበር። ወደ ንጉሡም ወደ ሰሎሞን መጥቶ ሥራውን ሁሉ ሠራ።

15፤ ሁለቱን የናስ አዕማድ አደረገ፤ የአንዱም ዓምድ ቁመት አሥራ ስምንት ክንድ ነበረ፥ የዙሪያውም መጠን አሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፤ የዓምዱም ውፍረት አንድ ጋት ነበረ፥ ውስጠ ክፍትም ነበረ። ሁለተኛውም ዓምድ እንዲሁ ነበረ።

16፤ በሁለቱም አዕማድ ራስ ላይ እንዲቀመጡ ከፈሰሰ ናስ ሁለት ጕልላት ሠራ፤ የአንዱም ጕልላት ቁመት አምስት ክንድ፥ የሁለተኛውም ጕልላት ቁመት አምስት ክንድ ነበረ።

17፤ በአዕማዱም ራስ ላይ የነበሩትን ጕልላቶች ይሸፍኑ ዘንድ ሁለት እንደ መርበብ ሥራ አደረገ፤ አንዱም መርበብ ለአንዱ ጕልላት ሁለተኛውም መርበብ ለሁለተኛው ጕልላት ነበረ።

18፤ ሮማኖችንም ሠራ፤ በአንድ ጕልላት ዙሪያ በተራ ሁለት መቶ ሮማኖች ነበሩ፥ በአንድም መርበብ ላይ ሁለት ተራ ነበረ፤ እንዲሁም ለሁለተኛው ጕልላት አደረገ።

19፤ በወለሉም አዕማድ በነበሩት ጕልላቶች ላይ የሱፍ አበባ የሚመስል ሥራ አራት ክንድ አድርጎ ቀረጸ።

20፤ በሁለቱም አዕማድ በነበሩት ጕልላቶች ላይ በመርበቡ ሥራ አጠገብ ሮማኖቹን አደረገ።

21፤ አዕማዱንም በመቅደሱ ወለል አጠገብ አቆማቸው፤ የቀኙንም ዓምድ አቁሞ ያቁም ብሎ ጠራው፤ የግራውንም ዓምድ አቁሞ በለዝ ብሎ ጠራው።

22፤ በአዕማዱም ራስ ላይ የሱፍ አበባ የሚመስል ሥራ ነበረ፤ እንዲሁም የአዕማዱ ሥራ ተጨረሰ።

23፤ ከፈሰሰም ናስ ከዳር እስከ ዳር አሥር ክንድ፥ ቁመቱም አምስት ክንድ፥ በዙሪያውም ሠላሳ ክንድ የሆነ ክብ ኵሬ ሠራ።

24፤ ከከንፈሩም በታች ለአንድ ክንድ አሥር ለአንድ ክንድም አሥር ጉብጉቦች አዞረበት፤ እርሱም በቀለጠ ጊዜ ጉብጉቦቹ በሁለት ተራ ከእርሱ ጋር አብረው ቀልጠው ነበር።

25፤ ኵሬውም በአሥራ ሁለት በሬዎች ምስል ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ከእነርሱም ሦስቱ ወደ ሰሜን፥ ሦስቱም ወደ ምዕራብ፥ ሦስቱም ወደ ደቡብ፥ ሦስቱም ወደ ምሥራቅ ይመለከቱ ነበር። ኵሬውም በላያቸው ነበረ፥ የሁሉም ጀርባቸው በስተ ውስጥ ነበረ።

26፤ ውፍረቱም አንድ ጋት ነበረ፤ ከንፈሩም እንደ ጽዋ ከንፈር ተሠርቶ ነበር፤ እንደ ሱፍ አበባዎች ሆኖ ተከርክሞ ነበር። ሁለት ሺህም የባዶስ መስፈሪያ ይይዝ ነበር።

27፤ አሥርም የናስ መቀመጫዎች ሠራ፤ የአንዱም መቀመጫ ርዝመት አራት ክንድ፥ ወርዱም አራት ክንድ፥ ቁመቱም ሦስት ክንድ ነበረ።

28፤ የመቀመጫውም ሥራ እንዲህ ነበረ፤ በክፈፎችም መካከል ያለው ሰንበር ይመስል ነበር።

29፤ በክፈፎቹም መካከል በነበሩ ሰንበሮች ላይ አንበሳዎችና በሬዎች ኪሩቤልም ነበሩ፤ እንዲሁም በክፈፎቹ ላይ ነበረ፤ ከአንበሳዎቹና ከበሬዎቹ በታች ሻኵራ የሚመስል ተንጠልጥሎ ነበር።

30፤ በየመቀመጫዎቹም ሁሉ አራት የናስ መንኰራኵሮች ነበሩባቸ፤ መንኰራኵሮቹም የሚዞሩበትን የናስ ወስከምት ሠራ፤ ከመታጠቢያውም ሰን በታች በአራቱ ማዕዘን በኩል አራት በምስል የፈሰሱ እግሮች ነበሩ።

31፤ በክፈፉም ውስጥ የነበረ አንገት አንድ ክንድ ነበረ፤ አንገቱም ድቡልቡል ነበረ፥ ቁመቱም ክንድ ተኩል ነበረ። በአንገቱም ላይ ቅርጽ ነበረበት፤ ክፈፉ ግን አራት ማዕዘን ነበረ እንጂ ድቡልቡል አልነበረም።

32፤ አራቱም መንኰራኵሮች ከሰንበሮቹ በታች ነበሩ፤ የመንኰራኵሮቹም ወስከምት በመቀመጫው ውስጥ ነበረ፤ የመንኰራኵሩም ቁመት ክንድ ተኩል ነበረ።

33፤ የመንኰራኵሮቹም ሥራ እንደ ሰረገላ መንኰራኵር ነበረ፥ ወስከምቶቹና የመንኰራኵሮቹ ክፈፍ ቅትርቶቹም ወስከምቱም የሚገባበት ቧምቧ ሁሉ በምስል የፈሰሰ ነበር።

34፤ በእያንዳንዱም መቀመጫ በአራቱ ማዕዘን በኩል አራት ደገፋዎች ነበሩ፤ ደገፋዎቹም ከመቀመጫው ጋር ተገጥመው ነበር።

35፤ በመቀመጫውም ላይ ስንዝር የሚሆን ድቡልቡል ነገር ነበረ፤ በመቀመጫውም ላይ የነበሩ መያዣዎችና ሰንበሮች ከእርሱ ጋር ይጋጠሙ ነበር።

36፤ በመያዣውና በሰንበሮቹ ላይ ኪሩቤልንና አንበሳዎችን የዘንባባውንም ዛፍ እንደ መጠናችው ቀረጸ፥ በዙሪያውም ሻኵራ አደረገ።

37፤ እንዲሁ አሥሩን መቀመጫዎች ሠራ፤ ሁሉም በምስልና በመጠን በንድፍም ትክክሎች ነበሩ።

38፤ አሥሩንም የናስ መታጠቢያ ሰን ሠራ፤ አንዱ መታጠቢያ ሰን አርባ የባዶስ መስፈሪያ ያነሣ ነበር፤ እያንዳንዱም መታጠቢያ ሰን አራት ክንድ ነበረ፤ በአሥሩም መቀመጫዎች ላይ በእያንዳንዱ አንድ አንድ መታጠቢያ ሰን ይቀመጥ ነበር።

39፤ አምስቱንም መቀመጫዎች በቤቱ ቀኝ፥ አምስቱንም በቤቱ ግራ አኖራቸው፤ ኵሬውንም በቤቱ ቀኝ በአዜብ በኩል አኖረው።

40፤ ኪራምም ምንችቶችንና መጫሪያዎችን ድስቶችንም ሠራ፤ ኪራምም ለንጉሡ ለሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት የሠራውን ሥራ ሁሉ ጨረሰ።

41፤ ሁለቱም አዕማድ፥ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ኩብ የሚመስሉትን ጕልላቶች፥ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጕልላቶች የሚሸፍኑትን ሁለቱን መርበቦች፥

42፤ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጕልላቶች ይሸፍኑ ዘንድ ለእያንዳንዱ መርበብ በሁለት በሁለት ተራ አድርጎ ለሁለቱ መርበቦች አራት መቶ ሮማኖች አደረገ።

43፤ አሥሩንም መቀመጫዎች፥ በመቀመጫዎችም ላይ የሚቀመጡትን አሥሩን መታጠቢያ ሰን፥

44፤ አንዱንም ኵሬ፥ ከኵሬውም በታች የሚሆኑትን አሥራ ሁለቱን በሬዎች፥

45፤ ምንቸቶቹንም፥ መጫሪያዎቹንም፥ ድስቶቹንም አደረገ። ኪራምም ለንጉሡ ለሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት የሠራው ይህ ዕቃ ሁሉ የጋለ ናስ ነበረ።

46፤ በዮርዳኖስ ሜዳ በሱኮትና በጸርታን መካከል ባለው በወፍራሙ መሬት ውስጥ አስፈሰሰው።

47፤ ሰሎሞንም ዕቃውን ሁሉ ሳያስመዝን አኖረ፤ የናሱም ሚዛን ከብዛቱ የተነሣ አይቈጠርም ነበር።

48፤ ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን ዕቃ ሁሉ አሠራ፤ የወርቁን መሠዊያ፥ የገጹም ኅብስት የነበረበትን የወርቅ ገበታ፥

49፤ በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት አምስቱ በቀኝ አምስቱም በግራ የሚቀመጡትን ከጥሩ ወርቅ የተሠሩትንም መቅረዞች፥ የወርቁንም አበባዎችና ቀንዲሎች መኰስተሪያዎችም፥

50፤ ከጥሩ ወርቅም የተሠሩትን ጽዋዎችና ጕጠቶች፥ ድስቶቹንና ጭልፋዎቹንም፥ ማንደጃዎቹንም፥ ለውስጠኛውም ቤት ለቅድስተ ቅዱሳን ደጆች ለቤተ መቅደሱም ደጆች የሚሆኑትን የወርቅ ማጠፊያዎች አሠራ።

51፤ እንዲሁ ንጉሡ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ያሠራው ሥራ ሁሉ ተፈጸመ። አባቱም ዳዊት የቀደሰውን፥ ብርና ወርቅ ዕቃም፥ ሰሎሞን አገባ፥ በእግዚአብሔርም ቤት ውስጥ በነበሩ ግምጃ ቤቶች አኖረው።